አቶ ታየ ደንደዓ የደንህንነት ስጋት እንዳለባቸው ነገር ግን ፈርተው ዝም እንደማይሉ ገለጹ

የጨፌ ኦሮሚያ አባል እና የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ አቶ ታዬ ደንደኣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከፍተኛ የጸጥታ፣ የሰብዓዊ  እና የፖለቲካ ቀውስ መኖሩን ገለጹ። የክልሉ መንግስት ክልሉን ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ ከመክተት ባለፈ የጨፌ ኦሮሚያ አባላትን እስከማስፈራራት ደርሷል ያሉት አቶ ታዬ ደንደኣ የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት የክልሉ ባለስልጣናት የጨፌ ኦሮሚያ አባላትን በስድስት ቡድን ከፍለው አቅጣጫ ሲሰጡና ሲያስፈራሩ እንደነበርም ጨምረዋል።

መደበኛው ጉባኤ ላይ እንዳይናገሩ መደረጋቸውን ያነሱት ሚኒስትር ዴታው «የመናገር መብት ከሌለ ሌላ መብት የለም» ካሉ በኋላ «የተከበረው ጨፌ አባል እና የብልግና ከፍተኛ አመራር የሆነን ሰው የመናገር መብት የነፈገ አመራር የማንንም መብት ሊያከብር አይችልም ዲሞክራሲንም ይገነባል ተብሎ አይጠበቅም ያሉ ሲሆን፣ “ እኔ በአጀንዳዉ ላይ ተቃዉሞ ለማሰማት እጄን ያወጣዉ ቢሆንም እጄ ስላልታየ አጀንዳዉ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል ተባለ፣ አንድ አንድ እጆች ደግሞ ባይወጡም ሲታዩ ነዉ የዋሉት” በማለት በስብሰባው አዳራሽ በአጀንዳው መጽደቅ ላይ ድጋፍ ያልሰጡ ቢሆንም  “በሙሉ ድምፅ ጸድቋል መባሉንም  ተናግረዋል። 

«የጨፌው ስብሰባ ሶስት አጀንዳዎችን በአንድ ላይ አደባልቆ የያዘዉ ሲሆን እነሱም ያለፈዉ አመት ሪፖርት፡ የሚቀጥለዉ ዓመት እቅድ እና ያለፈዉ ዓመት ተጨማሪ ባጀት ናቸዉ፤ ሶስት አጀንዳዎችን አንድ ላይ ደባልቀዉ ማፀደቅ ግልፅነትና እና ንፁነትን ሸፋፍኖ ማለፍ ነዉ» ያሉት አቶ ታየ አክለውም «አንድ ሰዉ ተጨማሪዉን ባጀት ተቃዉሞ የቀጣዩን ዓመት እቅድ ሊደግፍ ወይም ሪፖርቱን ደግፎ እቅዱን መቃወምም የሚችለበት እድል በመኖሩ በምንም መስፈርት ሶስት አጀንዳዎችን አንድ ላይ ቀላቅሎ ድምፅ ማሰጠት ትክክል እንዳልሆነም ገልሰዋል።

ከሁሉም ቀዳሚው አጀንዳ የሰላምና ተጠያቂነት ጉዳይ መሆን ይገባዋል ነበር ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት አቶ ያተ ሲቀጥሉ፣ «ባለፈዉ ዓመት በተመሳሳይ ወቅት በአጭር ጊዜ ዉስጥ ሰላም እናወርዳለን ተብሎ ነበር፣ የቀረበዉ ሪፖርት ደግሞ ቁጥራቸዉ ትንሽ የማይባል ሰዎች እጅ ሰጥተዋል፡ ልዩ ልዩ መሳሪያዎች ተይዘዋል፡ የተዘጉ መንገዶች መከፈታቸዉን እና በጠላት እጅ የነበሩ ዉስን ቀበሌዎች ተለቀዋል» የሚል የጥቅል ሪፖርት መሆኑን ጠቅሰው፡ በአሃዝ ማስቀመጥ ያልተቻለዉ ለምንድነዉ? ይሄ ሪፖርት ባለፈዉ ዓመት ተይዞ ከነበረዉ እቅድ አንፃር እንዴት ነዉ የሚታየዉ? ምን ነበር የታቀደዉ ከዚያ ዉስጥ ምን ያህሉን መፈፀም ተቻለ? በጥቂት ቀናት ዉስጥ ይረጋገጣል የተባለውን ሰላምስ በዓመቱ እንኳን ለማረጋገጥ እንዴት ተሳነን ማ ን ምን መፈፀም ሳይችል ቀረ? በህግ የተሰጠዉን ሀላፊነት ያልተወጣ ሰዉስ ለምነድነዉ በህግ የማይጠየቀዉ? የሚሉ ጉዳዮችን ያላሟላ በመሆኑ ሪፖርቱ ለጨፌው የማይመጥን ነው» ብለዋል።

በዚህ ዓመት 8 ዞኖች የሰላም እጦት ችግር ዉስጥ  ይገኛሉ ያሉት አቶ ያተ ደንደዓ፣ በህዝባችን ላይ የደረሰዉ ጉዳት በሪፖርቱ ዉስጥ አልተካተተም፡፡ ከጥር ወር ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ስንት ንፁህ ዜጋ ነዉ የተገደለዉ ስንት ሰዉ ነዉ አካሉ የጎደለዉ? ስንቱ ነዉ ከቤት እና ንብረቱ ተፈናቅሎ እየተንገላታ ያለዉ? ስንት የደሃ ቤቶች ናቸዉ የተቃጠሉት? ስንት የድሃ ከብቶች ናቸዉ የታረዱት? ስንት ወንድ እና ሴት ናቸዉ የተደፈሩት? የወደመዉ የመንግሰት እና የግል ንብረት ምን ያህል ነዉ ? ሰላም ማስጠበቅ እንኳን ባይቻል ይሄን ጉዳት አቀናብሮ ማቅረብ እንዴት ይከብዳል? ሲሉም ይጠይቃሉ፣ አክለውም በውይይቱ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች አስደንጋጮች ስለመሆናቸው ይጨምራሉ።

የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገመቺስ ደበላ ከሚያዝያ ወዲህ ባለው ጊዜ በምዕራብ ዋለጋ ብቻ 1105 ኦሮሞወች መገደላቸውን፣ 28 አመራሮች በአንድ ቀን መገደላቸውን እና ከ3 ቢሊየን በላይ ንብረቶች ላይ ውድመት ስለመድረሱ የተናገሩትን በማስታወስ፣ ይህ በኦሮሞዎች ላይ የደረሰው ጥፋት ግን በዞኑ በሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥፋት ትክክል እንደማያደርገውም ጨምረው ገልጸዋል፣ የመንግስት ሃላፊነት ሁለቱንም ወገኖች መጠበቅ መሆኑን በማንሳት። 

አቶ ታዬ አለኝ ያሉት መረጃ ጠቅሰው ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በሰሜን ሸዋ 210 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን፣ 109 አካል ጉዳተኛ መሆናቸውን፣ 526 ቤቶች በእሳት መቃጠላቸውን፣ 410 የአርሶ አደር በሬዎች መታረዳቸውን፣ 1.5 ቢሊዮን ብር በጥሬ መመዝበሩን፣ 195 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው 75,000 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ገልጸው፣ በቅርበት ቢመረመር ጉዳቱ ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችላል ያሉት አቶ ታዬ በጉጂ እና በወለጋ፣ በምእራብ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖችስ ምን ያህል ጉዳት ደረሶ ይሆን? ሲሉም ጠይቀው፣ በጨፌው ስብሰባ ወቅት የቀረበው ሪፖርት ይህንን ሁሉ እውነት የደበቀ መሆኑን አስረድተዋል።

ሴራ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ከባድ የፖለቲካ በሽታዎች ግንባር ቀደም መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታየ፣ ለእኔ መደመር አስፈላጊ ነዉ፣ የመደመር መርሆች ደግሞ ወንድማማችነት፣ ብዝሃነት እና ነፃነት ናቸው ካሉ በኋላ፣ አንዳንዶች ግን ከወያኔ በወረሱት ሴራ እና ስቃይ ይኮራሉ፣ “ፖለቲካ ህዝብን የማሳሳት ቁማር ነው” ብለዉም በኩራት ይናገራሉ፣ እውቀት ማስመሰል እና ግራ ማጋባት ነው ብለውም ያስባሉ ሲሉም ተችተዋል። አቶ ታየ በዚህም ሳያበቁ  በዚህ የሴራ ጨዋታ መኩራራት ምንኛ አሳፋሪ ነዉ? እራሱን “ብልፅግና” ብሎ የሚጠራ ሰውስ እንዴት የወያኔ ባህሪ ተሸካሚ ሆኖ ይኮራል? ሲሉም በኦሮሚያ አመራሮች ዘንድ ተንሰራፍቷል ያሉትን የሴራ ፖለቲካ አውግዘው ይህ ስርዓት ከባድ ዋጋ ተከፍሎበት እንጂ በጨዋታ አልመጣም፣ ስለዚህ ከዚህ በኋላ የሴራ ፖለቲካን ለመሸከም አንፈቅድም ብለዋል።

የብልጽግና ከፍተኛ አመራርና የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ አቶ ታዬ ደንደኣ በዚህም አላበቁም፣ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ኮሚሽነር ሶሎሞን ታደሰ በነዚሁ የሴራ ፖለቲካ አራማጅ ቁማርተኛ ባለስልጣናት (በመንግሥት ሃይሎች) መገደላቸውን ጠቅሰው፤ «ተማሪው ከመምህሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል፣ እናም ከወያኔ ሴራ የተማሩ ሰዎች እኛንም ሊገድሉን ይችላሉ፣ ግን ሞት ለሰው ልጅ የማይቀር ነውና የህዝብን እውነት ለመናገር አንፈራም! ኮሚሽነር ሰለሞን ታደሰን ገድለው ኮማንደር ተስፋዬ ድንቁን ያቆሰሉት እና ህክምና የነፈጉ ሰዎች ለእኛም አይመለሱም» ሲሉ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አደባብሶ ያለፈውን ጉዳይ አፈንድተውታል። 

ምናልባት አንድ ጤነኛ ዜጋ ይህንን “ለምን ውስጥ አልተናገርክም?” የሚል ጥያቄ ቢያነሳ ጥያቄው ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታየ፣ ምላሽ ሲሰጡ «ዉስጥ ተወያይተን ቢሆን ኑሮ ይህ ነገር ባልሆነ ነበር፡ እኛም ጠንክረን ሀገርንም እናጠነክር ነበር፡ ነገር ግን ዉይይት እንዲኖር ብዙ ለምነን አልተሳካም፡ ምክንያቱም የዉስጥ ዉይይት ለማድረግ በሩ ዝግ ነዉ፡፡» በማለት በኦህዴድ ብልጽግና ውስጥ ያለው ሁኔታ አደገኛ እና ከላይ እንደሚታየው አለመሆኑን አስረድተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *